900 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገለፀ

በኢትዮጵያ ከቀያቸው ተፈናቅለው ከሚገኙ ዜጎች ውስጥ 900 ሺህ የሚጠጉትን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን መንግስት አስታውቋል፡፡

ከግጭት እና መፈናቀል ጋር በተያያዘ እስከ አሁን 1 ሺህ 300 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ዛሬ በሰጠው መግለጫ ያስታወቀው፡፡

በኢትጵዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከማንነትና የወሰን አስተዳዳር ጋር በተያያዘ ከቀያቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ዜጎችን አንድም ጊዜያዊ ሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ህዝብና መንግስት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ ከነባር የመከባበርና የባሀል እሴቶች ባፈነገጡ መልኩ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉን አንስቷል፡፡

እነዚህን ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ብሎም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ነው የገለፀው፡፡

መጭው የክረምት ወቅት እንደመሆኑ ተፈናቃዮች ለህመም እንዳይዳረጉ መንግስት 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመመደብ ዓለም አቀፍ የመድሃኒት ግዥ እየፈፀመ መሆኑን ያነሱት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለግጭትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ እና በዚህ ሂደትም በቀጥታ ተሳትፎ ያላቸውን አካላት ተለይተው በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እንደተከናወነም ገልፀዋል፡፡

ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥላቻ፣ ተፈናቃዮችን የገንዘብ ምንጭ አድርጎ መነገድ እንዲሁም መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥንቃቄ የጎደለው ዘገባን ማሰራጨታቻው ለግጭትና መፈናቀል ከተለዩ ችግሮች ውስጥ እንደሚጠቀሱ አቶ ንጉሱ ገልፀዋል፡፡

የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የገበታ መርሃ ግብር በተመለከተ በአዲስ አበባ ላይ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ለፕሮጀክቱ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ሀገራት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

የሸገር ገበታ መርሃ ግርብር በመጪው ግንቦት አስራ አንድ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚካሄድ ሲሆን ፕሮጄክቱን ለማጠናቀቅ ሶስት ዓመታትን እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡