የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጠ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  በጤና ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ  በሃገር አቀፍ መመሪያዎች፤ በጥቅማ ጥቅሞችና በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በቅርቡ ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከሃሪቱ ከተውጣጡ  3 ሺህ ከሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡  

በውይይቱ ወቅት የጤና ባለሙያዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል መፍትሄ ያገኙ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች በመግለጫው ተነስተዋል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ሲሆኑ በሃገሪቱ ላይ በቂ የጤና ባለሙያ አለ የሚባለው የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠው ዝቅተኛ ስታንዳርድ 4 ነጥብ 4 የጤና ባለሙያ ለ1 ሺህ ህዝብ መሆኑን አስታውሰው በኢትዮጵያ ያለው ግን 0 ነጥብ  8 ለ1 ሺህ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የሚመረቁ የጤና ባለሙያዎችን ለመቅጠር ክልሎችና ወረዳዎች በዚህ ዘርፍ  ላይ በጀታቸውን እንዲጨምሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በክልሎች እና በዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎች እየተማሩ የሚገኙ 3 ሺኅ 800 ሃኪሞች ደሞዝና ጥቅማጥቅም ከግንቦት ወር አንስቶ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይሸፈናልም ተብሏል፡፡

የስፔዛላይዜሽን ስልጠና ከዚህ ቀደም በመንግስት ብቻ የሚሰት እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቁመው አሁን ግን በግል እንዲማሩ መፈቀዱን ገልጸዋልለ፡፡

የሃኪሞችን የወጭ መጋራት በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሃኪሞች ቴምፖራሪያቸውን ለመውሰድ 440 ሺህ ብር መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን አሁን ግን ያለ ምንም ክፍያ ወስደው የወጪ መጋራቱን ብቻ እንዲሸፍኑ መወሰኑም ተገልጿል፡፡