ከፀሐይ የሚገኘውን ኃይል መጠቀም የሚያስችል የሙያ ማንዋል ጸደቀ

ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የሙያ ማንዋል ጸድቆ ወደ ስራ ሊገባ ነው፡፡

የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ፣ አግራ ኢትዮጵያና ሌሎችም በማንዋሉ ላይ በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

ማንዋሉን በማጽደቅ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሃይሉ ማንዋሉ በሙከራ ደረጃ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይነትም በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተግባራዊ እንደሚደረግም አቶ ታመነ ጠቁመዋል፡፡

ባለሙያዎች ሰልጥነው ወደ ተግባር በሚገባበት ጊዜ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል፡፡