የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት በአዲስ አበባ ታስቧል

የሩዋንዳ ላይ የተደረገው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት የሚዘክር የእግር ጉዞ በአዲስ አበባ ተካሄዷል፡፡

4 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ጉዞ ‹‹ትዉስታ -ህብረት -ህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን በኢፌዴሪ የዉጭ ጉዳይ ሚሲስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል፣ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና በኢትዮጵያ የሩዋንዳ ኤምባሲ አስተባባሪነት ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የቆየ ወዳጅነት እንዳለቸዉ ገልፀዉ፣ የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ለኢትዮጵያዉያን ትምህርት የሚሰጥ ክስተት ነዉ ብለዋል፡፡

በሩዋንዳ ግጭት ከ100 ቀናት ባልበለጡ ጊዜያት ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሩዋንዳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

የሩዋንዳ መንግስትና ህዝብ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረትና የመንፈስ ጥንካሬ ያለፈውን ክስተት ዳግም በማይከሰትበት ሁኔታ መማማሪያ አድርገውት ማለፍ ችለዋል፡፡

ህይወታቸው ካለፉት ሩዋንዳዊያን መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የቱትሲ ጎሳ ያላቸው ዜጎች በመሆናቸው የቱትሲ ጅምላ ጭፍጨፋ በሚል ከአለም አሰቃቂ ክስተቶች አንዱ ሆኖ ይታወሳል፡፡