ፖሊስ ኮሚሽን የከተማዋን ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተማዋን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸ፡፡

ኮሚሽኑ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በአምስት በተመረጡ ክፍለ ከተሞች ለወንጀል መንስኤ ናቸው ባላቸው 14 ስፍራዎች በመገኘት ድንገተኛ የፍተሻ እና የቁጥጥር ተግባር አከናውኗል፡፡

በቀንና በሌሊት ባደረገው ፍተሻም 11 ሽጉጦች ከ900 በላይ ደንብ ተላላፊ ተሽከርካሪዎችና እንዲሁም ለወንጀል መፈጸሚያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በተጨማሪም አደንዛዥ እፅና የኮንትሮባንድ እቃዎች ሊያዙ መቻላቸውን በኮሚሽኑ የወንጀል እና የትራፊክ አደጋ መከላከል ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አያይዘው እንደገለጹት ተቋሙ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል ሰሞኑን ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ኮድ 3- 37872 በሆነ ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሸከርካሪ በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀ መደበቂያ ውስጥ የገቡ 36 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ከመሰል 33 ካርታዎች ጋር፣ 96 የብሬን ጥይቶች እና ከ9 ሺህ 800 በላይ የክላሽንኮቭ ጥይቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በተጠርጣሪነት የተያዙት የመኪናው አሽከርካሪና ረዳቱ ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ኮሚሽኑ 20 ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር ተይዘው ምርመራ ላይ እንደሆኑም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም የበለጠ ለማስተማመን እና ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመቆጣጠር መሰል ድንገተኛ ፍተሻዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን ህብረተሰቡም ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ትብብር እንዲቀጥል ኮሚሽኑ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎችም ሰላምና ጸጥታን ሊያናጉ የሚችሉ ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቁን ኮሚሽኑ ለዋልታ በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡