የኦሮሚያ ክልል ለ7 ሺህ 29 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለ7 ሺህ 29 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ታራሚዎቹ ባሳዩት በጎ ምግባር ከዛሬ ጀምሮ ይፈታሉ ብለዋል፡፡

የይቅርታ ተጠቃሚዎቹ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡

በደን ጭፍጨፋ፣ በህገ ወጥ ንግድ፣ በህገ ወጥ  የሰዎች ዝውውር፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፉትን ኢንዲሁም በሴቶችና ህጻናት ላይ ወንጀል የፈጸሙ ታራሚዎችን ይቅርታው እንደማይመለከታቸው አቶ ሽመልስ አብራርተዋል፡፡

የይቅርታ ተጠቃሚ ታራሚዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ቂም በቀል እንዳይኖር አስቀድሞ እርቀ ሰላም የማውረድ ስራ ተሰርቷልም ተብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ ወንጀል የሚበዛባቸውን ጉዳዮች ጥናት በማድረግ የህግ ማሻሻያ ስራና ወንጅልን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለታራሚዎቹ የተለያዩ ስልጠናዎችና የምክር አገልግሎት መሰጠታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ታራሚዎቹ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ህብረተሰቡና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍና ትብብር ኢንዲያደርጉላቸውም ተጠይቋል፡፡