ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከዓለም ሽማግሌዎች ህብረት አባላት ጋር ተወያዩ

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በፀረ አፓርታይድ ታጋዩ እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ኔልሰን ማንዴላ ከተቋቋመው የዓለም ሽማግሌዎች ህብረት አባላት ጋር ተወያዩ።

በዚህ ልዑክ ውስጥ የኮሎምቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጁአን ማኑኤል ሳንቶስ እና የዓየርላንድ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሜሪ ሮቢንሰን ይገኙበታል።

ቡድኑ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆን፥ በጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የሚገኙበትን መጠለያንም ጎብኝቷል።

አባላቱ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በነበራቸው ቆይታም ሀገራዊ እና አካባቢያዊ የፖለቲካ፣ የልማት እና ኢኮኖሚ ጉዳዮችን አንስተው ተወያይተዋል።

የቀድሞ የሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችን በአባልነት የያዘው ህብረቱ ለዓለም ሰላም፣ ፍትህ እና ሰብዓዊ መበት መጠበቅ ይሰራል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን፣ የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በዚህ ስብስብ ውስጥ ይገኛሉ።