የመሬት ነክ ጉዳዮቻቸውን ለማስፈጸም መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮቻቸውን ለማስፈጸም እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ወደ ማዘጋጃ ቤት ሲሄዱ ከወራት በላይ እንደሚያመላልሷቸው የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎች እያንዳንዱ አገልግሎት የሚወስደው የጊዜና ሰዓት መጠን የተቀመጠ ቢሆንም ጉዳቸውን ለማስፈጸም ከተቀመጠለት ጊዜ በላይ በመውሰድ መጉላላታቸውን ተናግረዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የይዞታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ተክሌ ነዋሪዎቹ ያነሱትን ቅሬታ አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ ስራዎቹን በተቀመጠው መለኪያ መሰረት ለማከናወን ተያያዥ ጉዳዮች የሚፈጸምባቸው መስሪያ ቤቶች በአንድ ቦታ አለመገኘታቸው በፍጥነት ለመስራት እንዳላስቻላቸው ገልጸዋል፡፡

በህብረተሰቡ በኩልም ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ሳያሟሉ አገልግሎት ለማግኘት በክፍለከተማው መገኘት ሌላው ችግር መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በሰራተኞች በኩል የሚፈጸም በደል ሲኖር እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡