ማህበሩ 29 የኩላሊት ህሙማንን ከግንቦት 15 ጀምሮ በነጻ እንዲታከሙ አደረገ

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒል የኩላሊት እጥበት ህክምና ሲከታተሉ ለነበሩ 29 ህሙማን ከግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በነጻ እንዲታከሙ አደረገ፡፡

ማህበሩ ከተመሰረተ 8 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የኩላሊት እጥበት ማእከል እንዲከፈት ያስቻለ ማህበር ነው፡፡

ድርጅቱ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩ ዜጎች ነጻ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንዲያገኙ ሲያደርግ መቆየቱ ነው የተገለጸው፡፡

የኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎቱን ከፍለው መጠቀም ላልቻሉ ዜጎች አገልግቱ ተደራሽ እንዲሆን በማስቻል የህክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚለምኑ ከ20 በላይ ዜጎችን የኩላለት እጥበት አገልግሎትን በነጻ እንዲያገኙና አገልግሎቱ ህሙማኑ ንቅለ ተከላ የማድረግ እድል እስኪያገኙ ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር በሃገሪቷ ከሚገኙ የግል እና የመንግስት ባንኮች ጋር በመሆን ሰራተኞች በሚያዋጡት መዋጮ በህመሙ የሚሰቃዩ ወገኖችን ለመርዳት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ መንግስትም ለህሙማኑ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በዘውዲቱ ሆስፒታል ዋልታ ያነጋገራቸው የኩላሊት ህመምተኞች በበኩላቸው በኩላሊት ህመም ምክንያት ቤት ንብረታቸውን በመሸጥ በቀን እስከ 1500 ብር ድረስ ከፍለው ኩላሊታቸውን በሳምንት ሶስት ጊዜ ይታጠቡ እንደነበር ገልታ አሁን ያገኙት የነፃ እጥበት አገልግሎት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡