ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ በባህል ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ስር የሚገኙ የኪነ ጥበብ ተቋማትን ጎበኙ

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በመድናዋ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ስር የሚገኙ የኪነ ጥበብ ተቋማት ላይ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ለረዥም ጊዜያት ተቋማዊ ችግር ያለባቸውን፣ ከይዞታ ጋር የተያያዘ ችግር መፍትሄ ያልተሰጣቸውን እና ፈፅመው በመረሳት እድሳት ሳይደረግላቸው የቆዩ ቴአትር ቤቶችን ከከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት እና አንጋፋ የዘርፉ ባለሞያዎች ጋር በመሆን ነው የጎበኙት፡፡

በመጀመርያ ከስምንት ዓመት በፊት የድሮ ህንፃው የፈረሰውን የራስ ቴአትር ቤትን የጎበኙ ሲሆን፣ የቀድሞ ይዞታው በመንገድ ግንባታ ምክንያት የተጣበበው የራስ ቴአትር የከተማ አስተዳደሩ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ በመልሶ ማልማት ወደ መሬት ባንክ ገቢ የተደረገው እና በተለምዶ አሜሪካ ጊቢ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ 4500 ካሬሜትር ቦታ ለዚሁ ማዕከል ግንባታ እንዲውል ወስኗል፡፡

ጉብኝታቸውን በመቀጠልም ለአፍሪካ የመጀመርያ የሆነው እና በርካታ የቴአትር ባለሞያዎችን ያፈራውን የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤትን ጎብኝተዋል፡፡

በዚህም የቴአትር ቤቱን ይዞታዎች በማሻሻል ታሪካዊ ቅርፁን ሳይቀይር ተጨማሪ አዳዲስ የማስፋፊያ ግንባታዎች እንዲደረጉም ተወስኗል፡፡

በመቀጠልም የግንባታ ሂደቱ በውል ወሳጅ ተቋራጭ ምክንያት የተጓተተውን የህፃናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤትን በመጎብኘት ቴአትር ቤቱ በፍጥነት ግንባታው እንዲጠናቀቅ እና አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር አሁን ያለውን ተቋራጭ ውል በማፍረስ ከሌላ ተቋራጭ ጋር አዲስ ውል እንዲፈራረም ተወስኗል፡፡

በመጨረሻም ኢንጅነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥበባት ኮሌጅን ጎብኝተዋል፡፡ 

በዚህ ጉብኝታቸውም በቴአትር እና የስነ ጥበብ ዲፓርትመንቶች ላይ ያለውን የመማሪያ ህንፃ እና የመሠረተ ልማት ችግር በሚቀረፍበት ሁኔታ ላይ ከባለሞያዎች እና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ተወያይተው አቅጣጫም መስጠቱን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡