የፍቼ ጫምበላላን በዓል ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

የዘንድሮን የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምበላላን በዓል በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የሲዳማ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ በዓሉን በድምቀት ለማክበር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፍቼ ጫምበላላ ከሲዳማ ብሄር ባለፈ በውስጡ በያዛቸው እሴቶች የዓለም ቅርስ ሆኖ በመመዝገቡ የበዓሉን እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የተለያዩ የህብረተስሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አዲስ አበባን ጨምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የበዓሉን እሴቶች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚካሄድ ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

የራሱ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት ባለቤት የሆነው የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በግንቦት 22 እና 23 በሀዋሳ ከተማ በድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ በዓሉ ላይ ለመታደም በርካታ እንግዶች ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ አለማት ወደ ስፍራው እንደሚጓዙም ታውቋል፡፡ 

የሰላም፣ የእርቅ እና የፍቅር በዓል እንደሆነ የሚነገርለት የፊቼ ጫምባላላ አከባበር ስነስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ነው፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የፍቼ ጫምበላላ በዓልን ከሃገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ከሚመጡ እንግዶቻቸው ጋር በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡