ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን አመራሮች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን አመራሮች ጋር በአዳማ ከተማ ተወያይተዋል።

በውይይቱም የግብርና ትራንስፎርሜሽን አመራሮች ግብርናን ለማዘመን ስላለባቸው ሃላፊነትና ሚና ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ በተያዘው ዓመት መኸር ወቅት ለግብርናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ የግብዓት አቅርቦቶችን በተገቢው ጊዜ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር አብይ ተናግረዋል ።

በተለይም ግብዓቶቹ በተገቢው ጊዜ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እንቅፋት እየፈጠረ ያለውን የሎጅስቲክስ አገልግሎት ችግር ለመቅረፍ ከሚለመከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ለዚህም በነገው ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ወደ ጂቡቲ የሚያቀኑ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈም በቀጣይ ዓመት ለአነስተኛ እና መካከለኛ መስኖ ልማት የሚውል 20 ቢሊየን ብር በጀት መያዙን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።

አመራሮቹ በበኩላቸው ብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት የድርጊት መርሃ ግብር በህዝቡ ዘንድ እንዲታወቅ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

መርህ ግብሩ 4 ቢሊየን ችግኞችን በመጭው የክረምት ወቅት ለመትከል ያሰበ መሆኑም ተገልጿል።

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በመቀነሱ በዚህ መርሃ ግብር 40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ መልሶ ለመትከል መታቀዱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።