በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች 525 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸው ተገለፀ

በኢትዮጵያ በሚገኙ አራት ክልሎች 525 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬተር ዶክተር በየነ ሞገስ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር በየነ በመግለጫቸው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ በኦሮሚያ፣በአማራና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መከሰቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአጠቃላይ 525 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ ተይዘዋል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።

በዚህ መሰረትም በኦሮሚያ ክልል በአራት ዞኖች ውስጥ 236 ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፥ ሁለት ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል ።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ 198 የሚሆኑ ሰዎች በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሲሆን፥14 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው አልፏል።

በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ደግሞ 13 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ነው ያሉት ዶክተር በየነ ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ9 ክፍለ ከተሞች በ40 ሰዎች ላይ የበሽታው ምልክት የታየባቸው መሆኑም ተገልጿል።

የበሽታውን መንስኤ በላቦራቶሪ ለማረጋገጥም ከተለያዩ አካባቢዎች በበሽታው ከተጠረጠሩ ታካሚዎች ናሙና መወሰዱን ዶክተር በየነ ተናግረዋል ።

ለዚህም ከኦሮሚያ ክልል 5፣ከአማራ ክልል 2፣ከትግራይ ክልል 2 እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ 10 በድምሩ የ19 ታካሚዎች ናሙና ተወስዷል ነው ያሉት።

በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቱ መሰረትም የበሽታው መንስኤ ዜብሮ ኮሌራ የተሰኘ ባክቴሪያ መሆኑን ነው ዶክተር በየነ የተናገሩት።

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልም እስካሁን ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች 13 የለይቶ ማከሚያ ማዕከላት መቋቋማቸው ተመላክቷል።

ካሳለፍነው መጋቢት ወር ጀምሮም የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለተፈናቃይ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት 847 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ተሰማርተዋል ።

በሽታው በተከሰተባቸው ሁሉም አካባቢዎች በቂ መድሃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦት እንዲከማች ተደርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፥ለማህበረሰቡም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አክለዋል ።

በከዚህ ባለፈም በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለወረርሽኑ ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የመለየት ስራ መሰራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።