በድጎማ ከውጭ የሚገቡ ዘይቶች በህብረተሰብ ጤና ላይ ችግር እንደሚያመጡ ተገለጸ

መንግስት በከፍተኛ ድጎማ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባቸው የሚረጉ ዘይቶች በጊዜ ሂደት በህብረተሰብ ጤና ላይ ችግር እንደሚያመጡ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በየአመቱ 450 ሺህ ቶን የረጋ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች፡፡ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ እነዚህ ዘይቶች የጥራት ደረጃቸው የተለየ ቢሆንም፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ግን በጥራም ሆነ በዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢባ አባተ ገልጸዋል፡፡

የሚረጋ ዘይትን ጥራት በተመለከተ በአይጦች ላይ አራት ወራትን የፈጀ ጥናት መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በጥናቱ መሰረት ዘይቱ የሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ መጠኑ የጨመረ በመሆኑ እንደየሰዎች የአጠቃቀም መጠን በጊዜ ሂደት የኮሌስትሮል ህመም መጨመርን ያስከትላል ብለዋል፡፡  

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የ16 ዓይነት ፈሳሽ ዘይቶች ያሉ ሲሆን፣ ሰባቱ በሀገር ውስጥ የሚመረቱና ቀሪዎቹ ዘጠኝ ደግሞ ከውጪ የሚገቡ ናቸው፡፡ በእነዚህ ፈሳሽ ዘይቶች ምርመራ የተካሄደ ሲሆን ከአመራረት ችግር በስተቀር ጤናን ሊጎዱ የሚችሉ ንጥረ ነገሮች እንደሌላቸውም ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታትና ከውጭ በሚገቡ ፈሳሽ ዘይቶች ላይ መንግስት ድጎማ በማድረግ ጥራት የሌላቸውን የዘይት ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መከላከል እንደሚያስፈልግ የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢባ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በሚረጉ ዘይቶች ይልቅ ፈሳሽ ዘይቶች ለጤናው የተሻሉ ናቸው ተብሏል፡፡በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ፈሳሽ ዘይቶች የአሲድ መጠን ቢኖራቸውም ጉዳታቸው እንደሚረጉ ዘይቶች አይደለም ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ 81 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ ከውጪ የሚገቡ የሚረጉ ዘይቶችን እንደሚጠቀሙም ተገልጿል፡፡

በዚህም ከልብ ጋር የተያያዘ ችግር የመምጣት አቅሙ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡