የመጫና ቱለማ የልማትና መረዳጃ ማህበር ለ4ኛ ጊዜ ተከፈተ

የመጫ ቱለማ መረዳጃ ማህበር ለአራተኛ ጊዜ መከፈቱን የፊታችን ሃምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ማህበሩ በመስቀል አደባባይ በሚገኘው ኤግዚቢሽን ማዕከል ይፋ ያደርጋል፡፡

የጅባትና መጫ መረዳጃ ማህበርን ከሸዋ ቱለማ መረዳጃ ማህበር ጋር አጣምሮ የተመሰረተው የመጫ ቱለማ የልማትና መረዳጃ ማህበር በወቅቱ የተሻለ ግንዛቤ በነበራቸው ግለሰቦች ስብስብ ሲቋቋም፣ ፍትሃዊ ያልነበሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክስተቶችን ለመለወጥ በማሰብም ነው፡፡

በተለይም የትምህርት የጤናና የመንገድ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚጎለብቱበት ስፍራ ማመቻቸት፣ ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ በማድረግ ብሔራዊ ሲቪላዊ መብታቸው ተከብሮላቸው እንዲሰሩ፣ ከዚህም አልፎ በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ተከፋፍሎ የነበረውን አስተሳሰብ ማስቀረት ከማህበሩ የምስረታ ውጥኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ውጭም የተለያዩ ብሔሮች በዚህ ማህብር ውስጥ ተካተው እንደነበር ታሪኩ ያትታል፡፡ ለአብነትም ማሞ ኮምቦልቻ ቆራቲ እና ኦብሴ ቡራቆ ከጌዴኦ፣ ሙሉ መጃ ከወላይታ፣ ወ/አማኑኤል ዱባለ ከሲዳማ፣ ፊታውራሪ ከታ ከኮንታ፣ ቀኛዝማች ቦጋለ ዋለሉ እና ቀኛዝማች ኤርታሞ እሬቻ ከጋሞ፣ ባላምበራስ ገብሬ ኦዳ ከቤንች፣ ባላምበራስ በሻ ጉዱ ከደዋሮ፣ ባላምበራስ አይዳ ሂሳሎ እና ቀኛዝማች ወ/ሚካኤል ገ/አብ ከአፋር ኢሳ፣ ቀኛዝማች ሐይሌ ዶናሞር ከሞቻ እንዲሁም ደጃዝማች አብዱራሂማን ሸህ ኦጀሌ ከቤኒሻንጉል ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ማህበሩ ላለፉት 55 ዓመታት በርካታ ውጣውረዶች ማለፉን የሚናገሩት የማህበሩ አመራሮች አሁን ላይ ከበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበራት ኤጄንሲ ህጋዊ እውቀት አግኝቶ እሩቅንም አልሞ ስራውን መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡

ማህበሩን ከምስረታው አራት ዓመታት በኋላ የገጠመው የመጀመሪያ ፈተና በ1959 ዓ.ም ነበር፡፡

የማህበሩ ንቁ መሪ እንደነበሩ ሚነገርላቸው የህግ ባለሙያና የሀረር አካዳሚ ተሸላሚ ምሩቅ እንዲሁም በኦሮሞ ታሪካ ላይ ትልቅ ጥናት በማድረግ መጽሃፍ በማዘጋጀት ላይ የነበሩ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር በሲኒማ ኢምፓየር ላይ ቦምብ ወርውሯል በሚል የሀሰት ክስ ተመስርቶባቸው በስቅላት እንዲገደሉና ያዘጋጁት የታሪክ ሰነድም እንዲቃጠል መደረጉ ይነገራል፡፡

ቀጥሎም በሀሰት ክስ ተጠይቀዋል የተባለላቸው አቶ ሀ/ማሪያም ገመዳ እና ጄነራል ዳዊት አብዲ በግርፋት መገደላቸውን የማህበሩ ድርሳን ያስረዳል፡፡

በወቅቱ መስራችና ፕሬዝዳንት የነበሩ ኮ/ል ዓለሙ ቄጤሳ ወደ ጎንደር፣ ማህበሩን ዘግይቶ ቢቀላቀሉም አቅም ሆነውት የነበሩት ጄነራል ታደሰ ብሩ ወደ ገለምሶ እንዲሁም የማህበሩ ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አቶ ሰይፉ ተሰማ ወደ ጋሞጎፋ በግዞት ተላኩ፡፡

ማህበሩ በ1985 ዓ.ም ዳግም ብከፈትም አልፎ አልፎ በመንግስት ላይ በሚያሰማው ተቃውሞ ከ11 ዓመታት በኋላ በ1996 ዓ.ም እንደገና ተዘጋ፡፡ በ1999 ማህበሩ ለሶስተኛ ጊዜ ቢከፈትም ያን ያህል ሳይገፋበት ከ2000 ዓ.ም በኋላ በርካታ ጉዳዮችን ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በማስተሳሰር አባላቱ ለእስር በመዳረጋቸው ማህበሩ ከእንቅስቃሴው ተገታ፡፡

ማህበሩ እንደልማት አጋር ሳይሆን እንደፖለቲካ ተቀናቃኝ መታየቱም አቀጭቾት መቆየቱን አመራሮቹ ያነሳሉ፡፡ ይሁንና መንግስት ይህን ማህበር እንደ አጋር እንጂ ለስልጣን ሽሚያ እንደ ተቋቋመ መታየትም የለበትም ያሉት አመራሮቹ ለተሻለ ውጤት ድጋፍንም ይጠይቃሉ፡፡

በወቅቱ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበራቸው እንደነ ጄነራል ታደሰ ብሩ እና ሀይለማሪያም ጋሪ ከማህበሩ አባላት ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

ማህበሩ በሃገሪቱ የሚስተዋሉትን ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በመወጠንም በወርሃ ግንቦት 1956 ተመሰረተ፡፡