የሰላምና ዴሞክራሲ ባህልን በመጠቀም ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተገለጸ

የሕዝቡን የሰላምና ዴሞክራሲን ባህል በመጠቀም ተጠቅሞ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል “ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ተገለጸ፡፡

የሰላምና ልማት ማዕከል የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከናሽናል ኢንዶመንት ፎር ዴሞክራሲ ከተሰኘ አለም ዓቀፍ ተቋም ጋር በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ሀገራዊ ለውጥና ፈተናዎችን፣ መጪው ሀገራዊ ምርጫና የተቋማት ግንባታ እንዲሁም ሚዲያን የተመለከቱ አምስት የመወያያ አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላምና ልማት ማዕከል ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ኢትዮጵያዊያን የራሱ የሆነ የባህልና የሰላም እሴት መገንቢያ መንገድ ያለ በመሆኑ ከውጭ ከሚመጡ መጤ ባህሎች ይልቅ ሀገር በቀል የሆነ ባህልና እሴት መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በአዕምሮና በልብ ጭምር መነጋገር የሚችሉ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም በአዕምሯችን ስንነጋገር ፍቅር ያለን ሰዎች ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያን መሰረታዊ ፍላጎት ከድህነት መውጣት መሆኑን ጠቁመው ልሂቃኑ ህዝቡን ሊረዱት ይገባል ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ተወካይ አቶ አብዲ ዘነበ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት የህዝብ አመኔታን እንዲያተርፍ መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ሀገር በቀል እሴቶችን በማጎልበት ኢትዮጵያዊ የዴሞክራሲ ባህል ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በዛሬው ውሎ በሶስት የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢዎች በተዘጋጀ “ኢትዮጵያ በፊትና አሁን” በሚሉ ርዕሶች በመወያት ላይ ይገኛሉ፡፡