ኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ ጥናቶች ያስፈልጓታል – ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

ነፃ እና ገለልተኛ ጥናቶች ለሀገር ልማት እና ኢኮኖሚ ያላቸው ድርሻ የጎላ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮነን ገለጹ፡፡  

“ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እና የለዉጥ አመራር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደዉን 3ኛው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረስ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መሰል አካዳሚዎች ነፃና ገለልተኛ ጥናቶች በማከናወን ለሀገር እና ለህዝብ የሚጠቅም የምርምር ስራ በማከናወን ኃላፊነታቸዉ ሊወጡ ይገባል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የምርምር ዉጤቶቹ ከመደርደሪያ ላይ ወርደዉ በየተቋሙ የሥራ መመሪያ እና የፖሊሲ ግብአት እንዲሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል፡፡

የመለስ ዜናዊ አካዳሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት አምባሳደር ዶክተር አዲስአለም ባሌማ በበኩላቸው አገር በፖለቲካ እዉቀት ላይ ተመሰርቶ እና በአግባቡ ከተመራ ለአገር ልማት እና ብልፅግና ያግዛል፤ አካዳሚዉም የምርምር እና ጥናት ስራዎችን በዚሁ አግባብ አጠናክረዉ እንደሚቀጥል ብለዋል፡፡

በኮንፈረሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የተፎካከሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ተመራማሪዎች እና የተቋሙ ሰራተኞች በተገኙበት ለሁለት ቀናት ይካሄዳል፡፡