የ2011 የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ

የ2011 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግኞችን በመትከልና የደም ልገሳ በማድረግ  ዛሬ በአዳማ ከተማ በይፋ ተጀመረ።

መርሃ ግብሩ በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አማካይነት በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶችና በጎ ፈቃደኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ የዓለም ጸጋዬ መርሃ ግብሩን ሲያስጀምሩ እንዳሉት፤ በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ13 ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡

በዚህም 12 ሚሊዮን ወጣት በጎ ፈቃደኞች በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንደሚሰማሩ ይጠበቃልም ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ላይ የሚሰማሩ አካላት ለሃገራቸው ያላቸውን ፍቅር ከፍ ከማድረጉም ባለፈ ህብረተሰቡንም በቁርጠኝነት እንዲያገለግሉ ተነሳሽነትን ይፈጥባቸዋል ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ታዳጊ ወጣቶች ከተለያዩ መጤ ልማዶች እና አደንዛዥ እጾች ለመታደግ ያለመ መድረክ እያከናወነም ይገኛል ፡፡