የጀኔራል አብርሃ ወ/ ማርያም (ኳርተር) የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ

የጀኔራል አብርሃ ወልደማርያም (ኳርተር) የቀብር ስነ ስርዓት በመቐለ ከተማ ተፈጸመ።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ቤተሰቦቻቸው፣ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ጨምሮ የክልሉ እና የፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

ለክብራቸውም 15 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

የጄኔራል አብርሃ አስክሬን ትናንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፥ አስክሬናቸው በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቤተሰቦቻቸው፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ወታደራዊ ባለስልጣናት በተገኙበት አቀባበል ተደርጎለታል።

ጀኔራል አብርሃ ወልደማርያም በጠና ታመው በታይላንድ ባንኮክ በሚገኝ አለም አቀፍ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ህይወታቸው አልፏል።

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን በእንዳባፃህማ ወረዳ እንዲጪዋ ቀበሌ ነሃሴ 21 ቀን 1953 ዓ.ም የተወለዱት ጀኔራል አብርሃም በ58 ዓመታቸው ነው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት።

ጄኔራል አብርሃ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከተራ ተዋጊነት እስከ ክፍለ ጦር አዛዥነት ድረስ በተለያዩ ውጊያዎች ሃላፊነታቸውን እንደተወጡ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ጄኔራሉ በ1983 ዓ.ም በመደበኛ የሰራዊት ግንባታ ከተጣለባቸው ሃላፊነት ጊዜ ጀምሮ በጡረታ እስከተሰናበቱበት ሃምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ መከላከያ ሲራዊት ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡

ጄኔራል አብርሃ ከሀገር ውስጥ ግዳጅና ተልዕኮ በተጨማሪ በሩዋንዳ አለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮም የመጀመሪያውን የጉና ሻለቃ በምክትል አዛዥነት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በፍፁም የህዝባዊ መንፈስ ተወጥተዋል፡፡

ጀኔራል አብርሃ ባለትዳርና የሁለት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ መረጃዉ የኤፍቢሲ ነዉ፡፡