የኢትዮጵያ ዉሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ዉሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዛሬ በአዳማ ከተማ መንግስታዊ ከሆኑ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ በዉሃዉ ዘርፍ አቅም ግንባታ ላይ ያተኮሩ ሁለት ሙያዊ ጽሑፎችን ጨምሮ ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላ የተመዘገቡ ለዉጦች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮች፣ በቀጣይ ለሚሰሩ የታቀዱ ተግባራት እንዲሁም ችግሮች ለመቅረፍ የተከናወኑ ስራዎች ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዉይይቱ ላይ የተገኙት የዉሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ወጌሾ እንዲሁም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ኃይሉ በዉሃዉ ዘርፍ አቅም ግንባታ ቴክኖሎጂ ሽግግር ሀገር አቀፍ ለዉጦች እየመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ በዉሃዉ ዘርፍ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባት እና በዘርፉ እየተሰጡ ያሉት ስልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሚኒስቴር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዉሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዉሃዉ ዘርፍ አቅም ግንባታ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የቴክኒካል ድጋፍ የሙያ ብቃት ምዘና እና የስፔሻላይዝድ ቤተሙከራ አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛ ሀገራዊ ተቋም ነው፡፡