በከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራ በይፋ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀመረ፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጀነር ታከለ ኡማ የክረምት የበጎ ፈቃድ ስራ አካል የሆነው የመንግስት ትምህርት ቤቶችን የማደስ ስራ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በክረምቱ የከተማ አስተዳደሩ ከ488 በላይ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ለማደስ በያዘው ዕቅድ መሠረት ነው ኢንጅነር ታከለ ኡማ የመነን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዕድሳትን በዛሬው ዕለት በይፋ ያስጀመሩት፡፡

የመነን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዕድሳት ወጪ ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን እና እድሳቱም በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የመነን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማ አስተዳደሩ የአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሆን በተወሰነው መሠረት ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ በትምህርታቸው ላቅ ያለ ውጤት ያመጡ 500 ሴት ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ይሆናል፡፡

ሁለቱ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች፣  የመነን እና ኢትዮ-ጃፓን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ የሆኑ የመማሪያ ክፍሎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መፅሐፍት እና ቤተ-ሙከራዎችን እንዲሁም የተመቻቹ የማደሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው ይሆናልም ነው የተባለው፡፡

በዕድሳት መርሃ-ግብሩ ላይ የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ፣ መምህራን እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቃኘው ሻለቃ አደባባይ አከባቢ በመገኘት የአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራ አስጀምረዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በአከባቢው ለረዥም ጊዜያት የአልጋ ቁራኛ የነበሩ አቅመ ደካማ እናት መኖሪያ ቤት ዕድሳት አስጀምረዋል፡፡

ዕድሳቱን በ10 ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ ለባለንብረቷ እንደሚያስረክቡም ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ-ግብር 1 ሺህ ለሚሆኑ አረጋዊያን ቤት የማደስ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ መረጃው የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ነው፡፡