በከተማ አስተዳደሩ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል የሆነው የሆስፒታል እድሳት ስራ ተጀመረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በተገኙበት የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል የሆነው የሆስፒታል እድሳት ተጀመረ፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ 13 ሆስፒታሎች ዕድሳት እና ጥገና ለማካሄድ የታቀደ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጥገና እና እድሳት ስራን ተጀምሯል፡፡

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ ቀደምት ሆስፒታሎች አንዱ ሲሆን፤ በሃገሪቷ የከፍተኛ ቀዶ ጥገና ህክምና ከመስጠት በተጨማሪ የጤና ባለሞያዎችን በማሰልጠን ትልቅ ግልጋሎት እየሰጠ ያለ ተቋም ነው፡፡

ኃላፊዎቹ በተጨማሪም ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውና ላለፉት በርካታ ዓመታት የውስጥም ሆነ የውጪ እድሳት ሳይደረግለት የቆየውን የጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሳት አስጀምረዋል፡፡

እድሳት የማስጀመር መርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ ህንጻውን ከማደስ በዘለለ ትምህርት ቤቱን ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ ስፍራ እናደርገዋለን ብለዋል፡፡

ከእድሳት ስራው በተጨማሪ ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤት እና የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ለተማሪዎች እንደሚገነባም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ኢ/ር ታከለ ኡማ፣  የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን፣ ከከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃለፊዎች እና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ችግኝ መትከላቸውም ተገልጿል፡፡

የትምህርት ቤቱ አጠቃላይ እድሳት በዋሺንግተን ሜዲካል ሴንተር ባለቤት ዶ/ር ማርቆስ የሚሸፈን ይሆናልም ነው የተባለው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክረምት ወራት በከተማዋ ውስጥ ያሉ 488 የመንግስት ትምህርት ቤቶችን እድሳት ለማካሄድ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ መረጃው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ነው፡፡