ተመራቂ ተማሪዎች በሄዱት ሥፍራ ከማህበረሰቡ ጋር በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው ጠ/ሚ ዐቢይ ገለጹ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መሰኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ባስመረቀበት መርሀግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመራቂ ተማሪዎች በሄዱት ሥፍራ ከማህበረሰቡ ጋር በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ ልማት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተመራቂ ተማሪዎች በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው 9ሺህ 637 ተማሪዎችን ነው ዛሬ ያስመረቀው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ10 ኮሌጆችና 12 ትምህርት ቤቶቹ ያሰለጠናቸውን 9ሺህ 637 ተማሪዎች ያስመረቀ ሲሆን ከእነዚህም 2ሺህ 763 ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል።
ዩኒቨርሲቲው 5ሺህ 876 ተማዎችን በመደበኛ ፕሮግራም፣ የቀሩትን 3ሺህ 761 ተማሪዎችን ደግሞ በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ያስመረቀ ሲሆን ከእነዚህም 230ዎቹ በሶስተኛ ድግሪ የተመረቁ ናቸው።
ከእነዚህም 2ሺህ 085 ተማሪዎችን በማታ ፕሮግራም፣ 319 ተማሪዎችን በርቀት እንዲሁም 1ሺህ 995 ተማሪዎችን ደግሞ በክረምት ፕሮግራም ነው አሰልጥኖ ዛሬ ያስመረቀው።
በተጨማሪም ለአገሪቷ ሰፊ ግልጋሎት በመስጠት ለሚታወቁት ለተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እንዲሪስ እና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷል።
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አጠቃላይ ከ32 ዩኒቨርሲቲዎች 120 ሺህ ተማሪዎች እንደሚመረቁም ታውቋል፡፡