የፍትሕ ማሻሻያ ተግባራትን አፈፃፀም ለመደገፍ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

የኢፌዴሪ የፍትህና የሕግ ምርምር እና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፎሎው ሺፕ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የፍትሕ ማሻሻያ ተግባራትን አፈፃፀም ለመደገፍ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሟል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ 1071/2010 የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት መሰረት በማድረግ የፍትህ ማሻሻያ ተግባራትን አፈፃጸም ለመደገፍ፣ በፍትሕ አካላት አቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር፣ በፍትሕ መረጃና ዶክመንቴሽን የአሰራር ሥርዓትን ለማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ለመሥራት ነው የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን የተፈራረመው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን የኢፌዴሪ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እየከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ የዘርፉን  አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ይህ የመግባቢያ ሰነድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር  ያደረጉት የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፎሎው ሺፕ ዋና ዳይሬክተር ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ መንግስት በዘርፉ ላይ እያደረገ ያለውን ውጤታማ ስራ አድንቀው፣ በዚህ መንገድ ድርጅታቸው ከተቋሙ ጋር በቅንጅት በመስራት ዘርፉን ለማሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡