በኦሮሚያ በአንድ ወር እስከ 300 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሓምሌ 22 ቀን ከ200 እስከ 300 ሚልዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮዉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳባ ደበሌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሃገር ከሚተከለዉ 4 ቢልዮን ችግኝ ዉስጥ 2 ቢልዮኑ በኦሮሚያ እንደሚተከል ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ዉስጥም 1.9 ቢልዮን ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ቀሪዉ ግዥ እየተፈፀመ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉም ከ1 ሺህ በላይ የመተከያ ቦታዎች በጂፒኤስ የተለዩ ሲሆን፤ 53 ቦታዎች አዲስ አበባን ጨምሮ ከ150 እስከ 250 ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ ይተከላሉ ብለዋል፡፡

በዕለቱ በፌዴራል መንግስት ክልሉ 126 ሚሊዮን ችግኝ እንዲተከል ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ ይህም በግለሰብ ሲሰላ አንድ ሰዉ 40 ችግኝ ይተክላል ማለት ነዉ ብለዋል፡፡ ክልሉ ግን አንድ ሰዉ በዕለቱ ከ60 እስከ 65 ችግኞች እንዲተከል አቅዷል ነው ያሉት፡፡

በችግኝ ተከላዉ ላይ አባ ገዳዎች ፣ወጣቶች ፣ታዋቂ ግለሰቦችና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎችና ዲፕሎማቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከልሉ እስካሁን እያካሄደ ባለዉ የችግኝ ተከላ ከ1.1 ቢልዮን በላይ ችግኝ መትከሉንም አስታዉቋል፡፡