የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደርን ሳሚ ጃሚል አብዱላህ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያንና የሳውዲ አረቢያን  ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በሕዝብ ለሕዝብ ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እና በሳኡዲ አረቢያ መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን ያስታወሱት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሳኡዲ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል በመጠቀም በስፋት እንዲሳተፉ አምባሳደሩ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

አምባሳደር ሳሚ ጃሚል በበኩላቸው የሁለቱ አገሮችን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን በመግለጽ፤ የሳኡዲ ባለሀብቶች በአትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል ተጠቅመው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት ለባለሀብቶቹ እያደረገ ላለዉ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሀጅ ጉዞ ለማድረግ በዝግጅት ላይ በመሆናቸው ኤምባሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።መረጃውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው