የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ 212 ተማሪዎችን አስመረቀ

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 212 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ በመጀመሪያ ዲግሪና በከፍተኛ ዲፕሎማ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 1500 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል፡፡

በምርቀቱ መርሀ-ግብር ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞን አመራሮችና የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አፈወርቅ  እንደገለፁት በኢትዮፕጵያ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሰዉ ኃይል ልማት ላይ እየሰሩ ሲሆን፤ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ  በየአመቱ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በማስመረቅ  የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልዋፀል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለፃ ዩኒቨርሰቲዉ  በታርጫ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመረቁ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዉ ከመማር ማስተማር ፣ ከጥናትና ምርምር፣ ከማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ባለፈ የልህቀት ማዕከል መሆን እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች ከትምህርት በቀሰሙት እዉቀት ለሀገር እድገት ተግተዉ መስራት እንዳለባቸዉም ፕሮፌሰሩ አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በ1999 ዓ.ም በ 16 የትምህርት መርሀ-ግብር የጀመረዉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ላይ ከ35ሺ በላይ ተማሪዎች እያስተማረ እንደሚገኝና ከ 2001 ዓ.ም ወዲህ የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ 35 ሺ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ የቅበላ አቅሙን ለመጨመር  የማስፋፋያ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑንም ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል፡፡