የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 809 ተማሪዎችን አስመረቀ

የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በዲግሪ መረሓግብር በሆቴል ማኔጅመንትና በቱሪዝም መኔጅምንት እንዲሁም በተለያዩ ሙያዎች በደረጃ ያሰለጠናቸውን 809 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ያስመረቃቸው ሰልጣኞች ለኢንዱስትሪው ዕድገት የድርሻቸውን በመወጣት አስተዋጽኦቸውን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡

ለዋልታ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂዎችም በተመረቁበት ሙያቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ያለበት ከመሆኑ አንፃር ዘርፉ እንዲያድግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ተመራቂዎቹ ጠይቀዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ላለፉት 50 ዓመታት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡