ሃምሌ 22 ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር 54 ሚሊየን ብር ተመድቧል

በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ4 ቢሊዮን ችግኝ በላይ ለመትከል እቅድ መያዙ ይታወቃል፡፡ 

የዚህ አካል የሆነውና ሃምሌ 22 ቀን የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አሰፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

ሃምሌ 22 ቀን በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘው እቀድ የተሳካ እንዲሆን 54 ሚሊየን ብር መመደቡም ተገልጿል፡፡

ለዚህም 46 ሚሊየኑ ለክልሎች 8 ሚሊየኑ ደግሞ ለፌደራል ከተሞች እንደተመደበ የብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

በእለቱም ያጋጥማሉ ተብለው የታሰቡ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫም እንደተቀመጠላቸው የተነገረ ሲሆን÷ ይህም የተሳካ እንዲሆን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከማለዳው 12 ሰአት እሰከ ምሽት 12 በሚካሄደው በዚህ መርሃግብር ላይ እያንዳንዱ ዜጋም ሆነ ተቋማት በተዘጋጀለቸው ቦታ በመገኝት በባለሞያዎች በመታገዝ የችግኝ ተከላውን ማከናወን እንደሚገባቸውም ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ ያለው የደን ሽፋን 15 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱንና ይህንን ለማሻሻል የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀከትን ለማሳካት ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡