ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር ዐቢይ አህመድ በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተመዘገበውን ስኬት አስመልክተው ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ህብረተሰቡ በዕለቱ ለመከወን የተያዘውን እቅድ በማለፍ ላስገኘው አመርቂ ውጤት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ለአረንጓዴ አሻራ ስኬት ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።
በብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ትላንት ማምሻውን 12፡00 ላይ ሲገባደድ በዕለቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከለው አጠቃላይ የዛፍ ችግኝ መጠን 353 ሚሊየን 633 ሺህ 660 መሆኑን የዘመቻው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው እንዳለው በዕለቱ በመላ አገሪቱ ቢያንስ 200 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ባደረገው የተቀናጀ ርብርብ በዕለቱ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞችን ለመትከል መቻሉን ኮሚቴው ገልጿል፡፡
በዚህም ከዚህ ቀደም በአንድ ጀምበር 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል 1 ነጥበብ 3 ቢሊዮን ህዝብ ባላት ህንድ ተይዞ የቆየውን የድንቃድንቅ መዝገብ ክብረ ወሰን በ5 እጥፍ ገደማ ለማሻሻል ተችሏል።