የመቀንጨር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት መስራት ይገባል ተባለ

በኢትዮጵያ በህጻናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ችግሩ ባለባቸው ቦታዎች የበጀት ድጋፍ ማጠናከርና ዘርፉን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ዘርፎች ተቀናጅተው መስራት አለባቸው ተባለ፡፡

ለዚህ ስኬትም በኢትዮጵያ የችግሩን መንስኤዎች ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ችግሩ በሚታይባቸው ቦታዎች ጥናት ተደርጓል፡፡ ጥናቱን ያዘጋጁት “አክሽን አጌነስት ሃንገር” እና “ዋተር ኤይድ” የተባሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡

በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች በቅንጅት እና በመናበብ አለመስራት፣ የህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት፣ የበጀት እጥረት ችግሩ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ምክንያቶች እንደሆኑ በጥናቱ ተመላክተዋል፡፡

ህጻናት ጤናማ አዕምሮና አካል ኖሯቸው ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የዋተር ኤይድ የሴክተር ግንባታ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ጽጌሬዳ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

በንጽህና ጉድለት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎችን ከምንጫቸው ለማጥፋት በውሃና ሥነምግብ ላይ ትኩረት ያደረገ ግንዛቤ ለህብረተሰቡ መሰጠት ይኖርበታል ያሉት ደግሞ  የ”ዋሽ” ቴክኒካል ዳይሬክተር  አቶ ተክለማሪያም አያሌው ናቸው፡፡

በየደረጃው  ያሉ የአመራር አካላትና በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ተቋማት መረጃዎችን በመጋራትና በመናበብ ቢሰሩ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም የ”አክሽን አጌነስት ሃንገር” የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፓኖስ ናቭሮዚዲስ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ 39 በመቶ ያህል ህጻናት የመቀንጨር ችግር እንዳለባቸው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር 2030 የህጻናትን የመቀንጨር ችግር ከምድረገጽ ለማጥፋት ሃገራት ተስማምተው እየሰሩ ነው፡፡