የሻደይ አሸንዳ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በጋራ እየተሰራ ነው

የሻደይ አሸንዳ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የአማራና የትግራይ ክልሎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛት አብዩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት የሻደይ አሸንዳ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የትግራይና አማራ ክልሎች በቅንጅት እየሰሩ ነው።

በአማራና ትግራይ ክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበር መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፥ ሁለቱ ክልሎች በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ መስማማታቸውን አንስተዋል፡፡
በዓሉ “የኢትዮጵያ ልጃገረዶች ጨዋታ” በሚል ስያሜ በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርስነት ለማስመዝገብ በሁለቱ ክልሎች መካከል እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ምክክር ተደርጎ ስምምነት ላይ መደረሱን አክለዋል።

በዓሉ በቅርስነት ለመመዝገብ በሒደት ላይ መሆኑን ያነሱት አቶ ግዛት፥ ኢትዮጵያም በዓሉን በቅርስነት ለማስመዝገብ ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰዋል።

በዓሉ በአማራ ክልል በወረዳና በዞን ደረጃ ከነሃሴ 16 እስከ 18 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበር ሲሆን፥ በክልል ደረጃ ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ከነሃሴ 19 እና 20 ቀን በድምቀት የሚከበር መሆኑ መገለፁን የዘገበው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ነው።