553 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረብያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

በሳዑዲ አረብያ ጂዛን ግዛት ኢዋ እና ሲጂን ነዓም በተሰኙ እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ 280 ኢትዮጵያውያን ትናንት  ሀምሌ 25 ቀን 2011 ዓም ከሌሊቱ በ8፡30  ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ ከ5 ዓመት እስከ 30 ዓመት ድረስ እስር ተፈርዶባቸው የነበሩ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ መንግስት ጅዳ በሚገኘው የኢፌዲሪ ቆንስላ ጄነራል ጽ/ቤት በኩል የሳዑዲ መንግስት ምህረት እንዲያደርግላቸው በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፍያ ሲደርሱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮንሱላር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አቶ ዮሃንስ ሾዴ እና ሌሎች አካላት በተገኙበተ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በተመሳሳይ በጅዳ እና ጂዛን ግዛት ያለ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ይኖሩ የነበሩ 273 ኢትዮጵያውን ረቡዕ ሀምሌ 24 ቀን 2011 ዓም ምሽት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ከእነዚህ ተመላሾች ውስጥ 75ቱ ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ወንዶች ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተለያዩ ሀገራት በእስር ላይ የሚገኙ ኢትጵያውያንን በማስፈታት በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩም በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው  እንዲመለሱ  እየሰራ መሁኑን ለዋልታ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡