በወቅታዊ የሃይማኖት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ ተጀመረ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀዉና በወቅታዊ የሃይማኖት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ፡፡

በጉባኤዉ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አቡነጳጳስ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ የቤተክርስቲያኗ ቀኖና በአግባቡ ከተሰራበት መልካም አሰተዳደርና ፍትህን ለማስፈን ጉልህ ድርሻ አለዉ ብለዋል፡፡

መጪዉ አዲስ ዘመን በመሆኑ ምክኒያት ችግሮቻችንን ቀርፈን በአዲስ አስተሳሰብ መቀበል እንድንችል የሃይማኖት አባቶች ህዝቡን የማዘጋጀት ስራ መስራት ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤዉ ለ4 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሚስተዋሉ ወቅታዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ዉይይት እየተደረገ ነዉ፡፡

በቀጣይ ቀናትም የኢትዮጵያዉያን ወንጌላዉያን አብያተክርስቲያናት ህብረት፤የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስ፤ የኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች፤ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለምአቀፍ ቤተክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዉይይት እንደሚደረግባቸዉ ይጠበቃል፡፡