ኢ/ር ታከለ ኡማ ከዓለም የቱሪዝም ፎረም ፕሬዝዳንት ቡሉት ማግቺ ጋር ተወያዩ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከዓለም የቱሪዝም ፎረም ፕሬዝዳንት ቡሉት ማግቺ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም ተቋማቸው እ.አ.አ በ2020 የሚካሄደውን የዓለም የቱሪዝም ፎረም በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ እና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በከተማዋ የሚሰራውን ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና በከተማዋ ውስጥ ላሉ ታሪካዊ ቅርሶች ለሚደረገው እንክብካቤ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ አዲስ አበባን የMICE ማዕከል ለማድረግ በከተማዋ አዲስ ከተቋቋመው የኮንቬሽን ቢሮ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ እና ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ኢ/ር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ከተማዋ እ.አ.አ በ 2020 የሚዘጋጀውን የዓለም የቱሪዝም ፎረም ብታዘጋጅ ተጠቃሚ እንደምትሆን ተናግረዋል፡፡

አለም አቀፍ የቱሪዝም ፎረም የመሠሉ መድረኮችን በከተማዋ ውስጥ ማስተናገድ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተጨማሪ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እንደሚያደርጋትም ኢ/ር ታከለ ኡማ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይም በቅርብ የተቋቋመው የአዲስ አበባ የኮንቬንሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል መገኘታቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡