የኢትዮጵያና ኬንያ ተጎራባች ማህበረሶች የባህል እና ቱሪዝም ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

በኢትዮጵያ የኛንጋቶም እና በኬንያ የቱርካና እና ሌሎች ማህበረሰቦች የባህል እና ቱረዝም ፌስቲቫል በኬንያ ሊካሄድ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ተጎራባች ማህበረሰቦቸን ከባህል ባለፈ በጋራ ልማት፣ ሰላም እና ጸጥታ የሚጫወቱትን ፈርጀ-ብዙ ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዓላማውን ያደረገው ፌስቲቫሉ በኬንያ የቱርካና ክልል ዋና ከተማ ሎድዋር ከነሐሴ 8 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በኬንያ የኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በፌስቲቫሉ ዙሪያ የቱርካና ክልል አስተዳዳሪ ጆስፋት ናኖክ ጋር በትናንትናው ዕለት በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለም በውይይቱ ወቅት፤ሚሲዮኑ በኢትዮጵያ እና ኬንያ የጋራ ድንበር አካባቢ የሚገኙ አጎራባች እና በባህል እና ቋንቋ የሚወራረሱ ማህበረሶቦች ዘንድ ያለውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የቱርካና ክልል አስተዳዳሪ ጆስፋት ናኖክ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እና ኬንያ አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦች ግንኙነት ለዘመናት የዘለቀ እና በባህል እና ቋንቋ መወራረስ ጠንካራ መሰረት ላይ የተገበነባ መሆኑን ተናግረዋል።

የባህል መድረኩ ግጭቶችን ለማስወገድ፣ መግባባትን ለመፍጠር እና ልማትን ለማረጋጥ ይጠቅማልም ብለዋል።

የቱርካና የባህል ፌስቲቫል በሰሜን ምዕራብ ኬንያ በሚገኘው የቱርካና ካውንቲ አስተዳደር አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄድ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ በሚውጣጡ የአተከር ወይም የኛቴኬሪን ቋንቋ ተነጋሪ በሆኑት የኛንጋቶም፣ የቱርካና፣ የቶፖሳ፣የካራሞጆንግ፣ የጂ እና የቴሶ ህዝቦች ክበረ በዓል ሲሆን፤ በዕለቱ የሁለቱ ሀገሮች ባህሎች እና ሌሎች እሴቶች ለእይታ ይቀርቡበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ባደረሰን መረጃ መሰረት ኤምባሲው በሚያዚያ 2011 ዓ.ም. በቦማስ ኦፍ ኬንያ የቱሪስት መንደር በተደረገው የቦረና ዓመታዊ የባህል ምሽት ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ መታደሙን አስታውሷል።