የአረፋ በዓል ሲከበር አቅመ ደካሞችን በማሰብና በመደገፍ ሊሆን ይገባል- ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል እምነቱ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካሞችን በማሰብና ያለው ለሌለው በማካፈል እንዲያከበር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢድሪስ አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢድሪስ 1 ሺህ 440ኛውን የአረፋ በዓል አስመልክተው ለሕዝበ ሙስሊሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢድ አል አድሃ አረፋ አላህ የነብዩ ኢብራሂምን ፍቅርና እምነት ለመፈተን ልጃቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዘበትን ዕለት ለማሰብ የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ነው።

ይህን ታሪክ ለመዘከር በዓሉ “የመስዋዕትነት በዓል” ተብሎ እንደሚጠራ የእምነቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ፤ የእምነቱ ተከታዮችም የነብዩ መሃመድን ፈለግ ተከትለው በዕለቱ እርድ ይፈጽማሉ።

ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብርም እምነቱ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካሞችን በማሰብ፣ ያለውን በማካፈልና በማስደሰት መሆን እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ አንድነትና ሠላምን ማስጠበቅ መሆኑን የጠቀሱት ሃጅ ኡመር እድሪስ “በአገርም ሆነ በውጭ ያለን ሁሉ አንድነታችንንና ሠላማችንን ልንጠብቅ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)