ወደ አብሮነትና ሠላም ፣ወደ አንድነትና ብልፅግና የሚመሩንን  ተግባራት ተግተን መፈፀም ይኖርብናል- ጠ/ሚ አብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ለ1 ሺህ 440ኛው ዓመተ ሒጅራ የኢድ-አል አድሐ (ዓረፋ) በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች በታላቅ ድምቀት በየዓመቱ ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓሎች መካከል ኢድ – አል አድሃ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ኢድ አል አድሃ የመስዕዋት (የእርድ) በዓልም በመባል ይታወቃል፡፡

በእስልምና የዘመን አቆጣጠር መሠረት የኢድ-አል ፍጡር በዓልን ተከትሎ ከአስር ሳምንታት ቦኋላ ወይም በአስራ ሁለተኛው የዙል ሂድጃ ወር ውስጥ የሚከበረው የዒድ-አል አድሃ በዓል የሐጅ ሥርዓት በሚከናወንባቸው አምስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ የሚካተት ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው፡፡

የኢድ አል አድሃ በዓል የተካተተበት የሐጅ ሥርዓት ታላላቅ ተምሳሌታዊ ዕሴቶችን ያቀፉ በርካታ ኩነቶችን አጣምሮ ከመያዙም ባሻገር ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች መካከል አንዱ የሆነውና ማንኛውም ሙስሊም የገንዘብና የጉልበት አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሊያከናውነው የሚገባውን የሀጅ ሥርዓትም ይፈፀምበታል፡፡

በዚህ አኳያ ኢድ አል አድሐ በዓል የተካተተበት የሀጅ ሥርዓት ዘርና ቀለም፣ ሃብታምና ደሀ፣ ሴትና ወንድ ተብሎ መለያየት ሳይኖር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ ሙስሊሞች በአንድ ሥፍራ፣ በአንድነት ፈጣሪያቸው ፊት በመቆም መራራቅን ሳይሆን መቻቻልን፣ ጠላትነትን ሳይሆን ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትን፣ ፀብና ሁከትን ሳይሆን ሠላምና ፍቅርን ከፍ በማድረግ መታዘዝንና መስዋዕትን በእምነትና በተግባር፣ በስሜትና በምግባር ከራሳችን ጋር የምናቆራኝበት ታላቅ የመታሰቢያ በዓል ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
ኢድ ሙባረክ!

በእስልምና የዘመናት ታሪክ ውስጥ ከነቢዩ ላህ ኢብራሂም እስከ ነቢዩ መሐመድ (ሠ.ዓ.ወ)፣ ከአደም እና ሐዋ እስከ አጀርና እስማኤል፣ በሕይወት እና ሞት፣ በሥጋዊ እና መንፈሳዊ ተምሳሌቶች እምነት እና ተስፋ፣ ፈተና እና ደስታ ጎልቶ የተገለፀበት ሀይማኖታዊ ሥርዓት ነው – ሐጅ፡፡

ይህን እውነታ የነቢያት ሁሉ ቀደምት አባት የሆኑት ነቢዩ ላህ ኢብራሂም (አላሂሰ ሠላም) በእርጅና እድሜ የታደሉት ልጃቸው እስማኤልን መስዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ በፈጣሪ መታዘዛቸው፣ በፈጣሪ ትዕዛዝ ቅስማቸው ቢሰበርም በእምነታቸው ጸንተው ትዕዛዙን ለመፈፀም መፍቀዳቸው በዚህም የተነሳ ፈጣሪ በልጃቸው ምትክ የሚታረድ በግ ያቀረበላቸው መሆኑ፣ በዚህም ከሀዘን ወደ ደስታ መሻገራቸውን አሳይቶናል፡፡

በመካ ዙሪያ ቀበሌዎች በሚገኙት በሳፋና በማርዋህ አነስተኛ ኮረብታዎች ሠባት ጊዜ በመመላለስ የሚከናወነው በፀሎት እና ዝክር የነቢዩላህ ኢብራሂም (አላሂሰ ሠላም) ሚስት ግብፃዊቷ አጃር ወይም አጋር ጡት ከሚጠባ ልጇ እስማኤል ጋር በብቸኝነት መሸሿ፣ በዚያ ምድረ-በዳ የሚላስ እህል የሚቀመስ ጠል አጥታ በሠፈያና በመርዋ ኮረብቶች መካከል መባዘኗ በምድረበዳ የዘምዘም ውኋ ምንጭ የፈለቀላት መሆኑ፣ ሌላም ሳይሆን ያንኑ እምነት እና ተስፋ፣ ፈተና እና ደስታ ማሳያ ተምሳሌት ነው፡፡

ዛሬም በሀገራዊው የለውጥ ጉዞና እርምጃ ተስፋ ማድረግን ሀብትና እምነቱ ያደረገ ሕዝብ በዚያው መጠን በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ተስፋ መቁረጥ ቢጫነው አይገርምም፡፡ ተስፋ መቁረጥ ግን ከፈተና አያድንም፡፡

ወገንንም ወደ ድል አያሻግርም፡፡ በእምነታቸው በፀኑ ዜጎች እንጂ በተስፋ ቆራጮች ሀገርና ሕዝብ ፈተናቸውን አልፈው መሠናክሉን ተሻግረው ለድልና ደስታ አይበቁም፡፡ በእንዲህ አይነቱ ወቅት ሀገርና ሕዝብ አሻጋሪና ሩቅ ተመልካች ባለራዕይ መሪ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ለሠላም እና ለፍትህ መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ የሆነ መሪ፡፡ ይህ ሲሆን በድካም ተሸንፈው በጉዞ መሐል የወደቁት እና በስብሰው አፈር ወደ መሆን ሊሸጋገሩ የተቃረቡት አፈራቸውን ከላያቸው በማራገፍ ቀጥ ብለው ዳግም አብረውን መጓዝ ይጀምራሉ፡፡

ሠላም ረዥሙ የታሪክ ጊዜ ነው። ችግሮቻችን ሁሉ በአንድ ጀንበር ሊፈቱ እንደማይችሉ ተገንዝበን፣ የጋራ ችግራችንን በጋራ ለመፍታት ቆርጠን ከተነሳን እንደ ነቢዩላህ ኢብራሂም እንደ አጋርና ኢስማኤል ዘመን ተሸጋሪ ሠላምና ብልፅግናን ማረጋገጥ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እጅግም ከባድ አይሆንብንም፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች!

በላቀ ደረጃ ሕብረትን፣ በልዩነት ምትክ አንድነት ከመነሻው አንስቶ እስከ መድረሻው የሚዘልቀው የኢድ አል አድሃ በዓል እና የሐጅ ሥርዓት ለእኛ ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን የመልካም ዕሴት መማሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥም ግለኝነትና ስግብግብነት፣ ጽንፈኝነትና ግትርነት፣ ሠፍቶ በተንሰራፋበት ወቅትና ዘመን መራራቅን ሳይሆን መቻቻልን፣ ጠላትነትን ሳይሆን ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትን፣ ፀብና ሁከትን ሳይሆን ሠላምና ፍቅርን ከፍ በማድረግ በእምነትና በተግባር፣ በስሜትና በምግባር ከእኛነታችን ጋር የሚያቆራኝ ሥርዓት እጅግ ሲበዛ አስፈላጊ ነው፡፡

በዚህ ረገድ፣ በሐጅ ሥርዓት ሶስተኛ ምዕራፍ የተካተተው የአረፋ ሥርዓት በአንድ በኩል ነቢዩ መሀመድ (ሠለላህ አላይህ ወሰላም) ምድርን ተሰናብተው ወደ ዘላለማዊ መኖሪያቸው ከማምራታቸው በፊት የመጨረሻውን የቁርዓን አንቀፅ በአረፋ ኮረብታ ማውረዳቸው ሲዘከርበት በሌላ በኩል ደግሞ የፍርድ ቀን መኖሩን እና በዚያም ወቅት ገላችንን ከምንሸፍንበት ጨርቅ ባሻገር አንድም ሀብት ንብረት እንደማይከተለን ማስታወሻ ነው፡፡

የአረፋ ሥርዓት ከዚህም በተጨማሪ አባታችን አደም እና እናታችን ሀዋ የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ በማጉደላቸው የተነሳ ከገነት ቤታቸው ወደ ምድራዊ ዓለም ተባረው ተለያይተው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አርዱል አረፋ ተብሎ በሚጠራው የአረፋ ኮረብታ ላይ መገናኘታቸው ‹አረፍኪኒ›‹አረፍቲኒ› መባባላቸው ይዘከርበታል፡፡

በትናንትና ጥፋት እና ስህተት ሳቢያ የሠው ልጅ በሕይወት ከተሳሰረው አካሉ ጋር ለዘለዓለሙ ተለያይቶና ተራርቆ መኖር እንደሌለበት ይልቁንም በንሰሃ፣ በይቅርታ፣ በምህረትና በእርቅ አብሮነትንና አንድነትን ማስቀጠል መልካም መሆኑን የሠው ልጅ መማር እንዲችል በአባታችን አደም እና በእናታችን ሀዋ (የየአርዱል አረፋ) በአረፋ ተራራ መገናኘት የተገለፀ ታላቅ ተምሳሌታዊ አስተምሮት ተደርጎም ይቆጠራል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን በትናንት አብሮነታችን ያስመዘገበናቸው በርካታ አኩሪ የጋራ ገድሎች እንዳሉን ሁሉ በትናንት ግንኙነታችን ውስጥ ፍቅርን፣ ፍትህና ርትዕን አጉድለንና ጎድሎብንም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ደግሞ በትናንት ታሪክ ውስጥ እድሜ ዘላለማችንን ተኝተን በማማረር ማሳለፍ መፍትሄ አይሆንም፡፡ በዛሬ ሕይወቱ ዳገት መውጣትን የሚፈራ ትውልድ በነገ ሕይወቱ ቁልቁለት መውረድ ሊጠብቀው አለመቻሉ ግልፅ ነው፡፡

ነገን በዛሬ ቀና ራዕይና መልካም ተግባር እንጂ በምንም መልኩ ብርሃን ማላበስ አይቻልም፡፡ ችግራችን ውስብስብ ቢሆንም መፍትሄም ያለው፣ እዚሁ የአብሮነት ባህላችን ውስጥ ነው፡፡ አብረን ከሆንን አንሰበርም፡፡ አብረን ከሆንን የማንፈታው ችግር አይኖርም፡፡ የእድገትና የብልጽግናችን ዋስትና ደግሞ እየተቋሰልንም ቢሆን አብረን ተዋደን እና ተከባብረን መኖራችን ነው፡፡

ለዓመታት ተከፋፍሎ የቆየው የሙስሊም ማኀበረሰብ ለውጡ የፈጠረለትን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አንድነቱን ለማጠናከር በጋራ መንቀሳቀስ በጀመረበት ማግስት የምናከብረው ይህ በዓል ደስታችንን እጥፍ ድርብ የሚያደርግልን ብቻ ሳይሆን ተስፋችንንም የሚያለመልም ነው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆነው ኀብረተሰባችን መካከል የሚፈጠር አንድነት ለሙስሊሙ ወገናችን ብቻ ሳይሆን ለሀገራችንም አንድነትና ጥንካሬ ምንጭ መሆኑን መንግስት እንደትናት ሁሉ ዛሬም አበክሮ ይገነዘባል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ዛሬም ድረስ ውስብብስብ እና ፋታ የማይሰጡ ችግሮች ባለቤቶች መሆናችን ከቶውንም ሊዘነጋን አይገባም፡፡ እነዚህ ችግሮቻችን እንኳንስ፣ ተለያይተንና ተከፋፍለን ቀርቶ፣ ተባብረን እና ተዋደንም ቢሆን ለመፍታት ዘመናት ያስፈልጉናል፡፡

ያን የመፍትሄ ዘመን በአዲሱ የለውጥ መንገድ ከዓመት በፊት አንድ ብለን እንደጀመርነው ሁሉ ከዚህ በኋላም የአብሮነትንና የአንድነትን ዋጋ በልኩ በመረዳትና በመገንዘብ ከቀድሞው በላይ የሚያራርቁንና የሚያቃቅሩንን፣ የሚያጠፋፉንን የሚያለያዩንን ተግባራት ሳይሆን በፍቅር፣ በይቅር ባይነት ወደ አብሮነትና ሠላም ፣ወደ አንድነትና ብልፅግና የሚመሩንን የመደመር ዕሳቤና ተግባራት ተግተን መፈፀም ይኖርብናል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ከትናንት ታሪኩ ትምህርት ወስዶ ከሚገኝበት ሀገራዊ የማንነት የቀውስ አዙሪት የሚወጣበትና ወደ እድገትና ወደ ብልፅግና ጎዳና መግባት የሚያስችለውን የቁጭት ስንቅ መሠነቂያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በእጃችን ውስጥ ባለው ዛሬ ተጠቅመን በመለያየት ሳይሆን በአርዱል አረፋ እንደተቀጠለው የአዳምና ሄዋን መገናኘት በአብሮነትና አንድነት ዘላለማዊ የድል ታሪክ የምንሰራ ትውልዶች ለመሆን እንድንተጋ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች!

በላቀ መደጋገፍ ታጅቦ ከጅማሮ እስከ ማክተሚያ የሚጓዘው በዓል ጠንካሮች ደካሞችን ፣ ባለፀጎች ምስኪኖችን፣ ወጣቶች አዛውንቶችና ሕጻናትን በዓሉ ላይ በሕብረት በመቆም፣ ከበዓሉ ቦኋላም መጠያየቅ፣ አብሮ ማሳለፍ ትልቅ ቦታም ይሰጠዋል፡፡

ከእኛ በዓቅም ያነሱ ወገኖቻችን በዓሉ ለእኛም ሆነ ለእነርሱ እኩል ቢመጣም በማጣታቸው ፣ጠያቂ በማጣታቸው የተነሳ በዓሉን በባዶ ሆድ እንዳያሳልፉ ከሱም በላይ ሳቅና ወግ ርቋቸው መተከዛቸውና ማዘናቸው ሊሰማንና ሊያሳዝነን ይገባል፡፡

ከዚሁ በተጓዳኝ ነቢዩ መሀመድ (ሠለላህ አለይህ ወሠለም) በተለያዩ ሀዲሶቻቸው አረንጓዴ አሻራን አትሞ ማለፍ ያለው ምንዳ ከሰደቃ ሊስተካከል እንደሚችል ከመግለፃቸው ባሻገር፣ “የመጨረሻው የፍርድ ቀን ሊዘረጋ ሠዓቱ የተቃረበ ቢሆን እንኳ እርሱ በእጁ የዛፍ ችግኝ የጨበጠ ሠው ቀሪዋ አንድ ሠከንድ እንኳ ብትሆን እርሷን ተጠቅሞ ችግኙን ይትከል” በማለት አስተምረዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሀገርና ሕዝብ በውዲቷ የሀገራችን ምድርና አፈር የአረንጓዴ አሻራችንን አሳርፈን ለማለፍ ቃል ተገባብተን በችግኝ መትከል እና መንከባከብ የጅማሮ ጉዞ ማድረጋችን ብዙም ያልደበዘዘ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከልነው የችግኝ ብዛት በራሳችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ሀገራዊ ስማችንን ከፍ ያደረገና በዓለም የላቀ ክንውን ክብረ ወሰን መዝገብ ማስፈርም ያስቻለን ታላቅ ታሪካዊ ዕለት ሆኖ አልፏል፡፡

ኢትዮጵያውያኖች ዛሬም እንደትናንቱ ከወሰኑና ከቆረጡ በአንድ ጀንበር በሚሊዮኖች በመትመም ያስቀመጡትን ዓላማና ግብ ከዳር ለማድረስ የማይሰንፉ ሕዝቦች መሆናችንን ዳግም ለዓለም ሕዝብ ያረጋገጥንበት እና ያስመሰከርንበት ትዕይንት መሆኑ ባይካድም በሀገር ደረጃ ካለብን የተከማቸ እና የዞረ ዕዳ አንፃር የአረንጓዴ አሻራ የማኖር ሥራችንን መጀመርን እንጂ መጨረስን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም መልካም ጅምራችንን አጠናክረን በመቀጠል የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴያችንን፣ በውኋ ማጠጣት፣ አረምን በማስወገድና መንከባከብ አጠናክረን እንቀጥል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በታሪካዊው ሐምሌ 22 ቀን ከተቀረው የሀገራችን የሌሎች እምነት ተከታዮችና ቤተሰቦች ጋር ጎን ለጎን በመቆም እና እጅ ለእጅ በመያያዝ እንደፈፀማችሁት የላቀ ገድል ሁሉ በቀጣዮቹ ጊዚያትም የጀመርነውን ሀገርን የማስዋብ ስራ አጠናክሮ በመቀጠል፣ ሀገራችሁን ከምድረ-በዳነት እና ከዙሪያ መለስ ብክለት ለመታደግ አረንጓዴ አሻራችሁን ደጋግማችሁ በማኖር የዜግነት ኋላፊነታችሁን እንድትወጡ ዳግም ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ተፈፃሚ እንደምታደርጉትም እተማመናለሁ፡፡

በመጨረሻም እንኳን ለኢድ አል – አድሃ በዓል በሠላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የደስታ የሠላም፣ የይቅርታ፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡

ኢድ ሙባረክ