ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለቡ ቫርኔሮ አከባቢ ሰሞኑን በፈረሰው አሊፍ መስጅድ በመገኘት የሀይማኖት አባቶችን አነጋገሩ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለቡ ቫርኔሮ አከባቢ ሰሞኑን በፈረሰው አሊፍ መስጅድ በመገኘት የሀይማኖት አባቶችን አነጋግረዋል፡፡

ኢንጅነር ታከለ ኡማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከከተማ አስተዳደሩ እውቅና ውጪ የፈረሰውን የአሊፍ መስጅድ ጎብኝተዋል፡፡

በዚሁ ጉብኝታቸውም ጥቂቶች በተንኮል ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ሊያጋጩ እና በሴራ ሊበትኑ ቢያስቡም እኛ ግን ችግሮችን በተሻለ መንገድ እናልፋቸዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማምለኪያ ቦታዎችን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከሁሉም የእምነት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

መስጅዱን በማፍረስ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎንም መስጅዱን በተሻለ ሁኔታ ለመገንባትም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ተለዋጭ ቦታም ለአዲስ አበባ መጅሊስ መተላለፉም ነው የተገለጸው፡፡

ከተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚያስተጋጉሉንን ለመግታት አሁንም የጋራ ጥረታችን ሊቀጥል ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከከንቲባው ጽ/ቤት የተኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡