1 ሺህ 440ኛው የአረፋ በዓል በመላ ሀገሪቱ ተከበረ

የ1440ኛው የዒድ አልአድሀ (አረፋ) በዓል በመላ አገሪቱ  በደማቅ ስነ ስርዓት ተከበረ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተወካይ ሼህ ሰዒድ አህመድ ሙስጠፋ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለአገራችን አንድነትና ለሰላም፣ ለአብሮነት በጉልበታችን፣ በእውቀታችንና በገንዘባችን የሚፈለግብንን ሁሉ ማበርከት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ በበኩላቸው፣ የአረፋ በዓል ለመላው የሙስሊም ማህበረሰብ የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሳብ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር የሙስሊሙን ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በዘላቂነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተወካይ አቶ ዮሃንስ ምትኩ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዘንድሮን የዒድ አልአድሀ በዓል ልዩ የሚያደርገው የሙስሊሙ አንድነት ከወትሮው በተለየ መልኩ የተጠናከረበት፣ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና በሃይማኖት አባቶች ያጋራ ጥረት በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶች የጠበቡበትና መቻቻል በታየበት ወቅት በድምቀት መከበሩ ነው ብለዋል፡፡(ኢቢሲ)