የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ይፋ አደረጉ፡፡

ፕሬዝዳንቷ ኢትዮጵያ በ2025 የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት አምስት አመታት ሲዘጋጅ የቆየውና በቀጣዮቹ አምስት አመታት የሚተገበር ሀገራዊ  የጸረ ሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ፍኖተ ካርታ በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል፡፡

በስነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ሴቶችን ለዕድሜ ልክ ችግር የሚዳርግ በመሆኑ፤ አሁን የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝኘት ያሳያል ብለዋል፡፡

ባለድርሻ አካትና ህብረተሰቡ ለፍኖተ ካርታው ስራ ስኬት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ያለም ፀጋይ በበኩላቸው፤ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ በመላው ሀገሪቱ ያለ ችግር መሆኑን አንስተዋል። ፍኖተ ካርታውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማከናወን  ሰፊ ማህበራዊ ንቅናቄ እንደሚደረግና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ፍኖተ ካርታውን ለማስፈጸም ሶስት ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግም በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡