ሦስት ዓመት የነበረው የዩኒቨርሲቲ የዲግሪ መርሀ ግብር ቆይታ ወደ 4 ዓመት ከፍ እንዲል ተወሰነ

ሦስት ዓመት የነበረው የዩኒቨርሲቲ የዲግሪ መርሀ ግብር ቆይታ ወደ 4 አመት ከፍ እንዲል ተወሰነ፡፡

በ2012 ዓ.ም ወደ መንግሥትም ሆነ የግል ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ አዲስ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩት በ15 አዳዲስ ትምህርቶች መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታውቋል።

በሦስት ዓመታት ይጠናቀቅ የነበረው የዲግሪ መርሀ ግብርም ወደ አራት ዓመት ከፍ እንደሚል ነው የገለጸው።

በዚህ ሂደት እንዲያልፉ የሚደረጉትም በ2012 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች እንደሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የሚሰጡት የትምህር ዓይነቶች ለሁሉም የትምህርት ክፍሎች የጋራ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡

ትምህርቶቹም ተማሪዎች በአስተሳሰብ ምጡቅ እንዲሆኑ፣ ብዝሀነትን፣ የሀገርን ባህል፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና ታሪክ እንዲያውቁ የሚያደርጉ ናቸው ብሏል ኤጀንሲው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት፣ ስነምግባር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት እንዴት ይቃኝ? በሚል ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በምሁራን ሰፊ ጥናት ሲደረግና ሕዝብም ሲወያይበት መቆየቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም አድማሴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስረድተዋል፡፡ በሂደቱም ማሻሻያ እና ለውጦች ተደርገዋል።

በዚሁ መሰረትም በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶችን መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሶ ለዚሁ ዝግጅት መደረጉን፣ አሁን ያለው ሁኔታም ትምህርቱን ለመጀመር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡