የፅዳት ዘመቻ ተግባር ባህል ሆኖ እንዲቀጥልና ህብረተሰቡ ለሀገራዊ ጥሪ የሚያሳየው ምላሽ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ

የፅዳት ዘመቻ ተግባር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እና ህብረተሰቡ ለሀገራዊ ጥሪ የሚያሳየው ምላሽ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ፡፡

አራተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት ተከናውኗል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ይፋ በተደረገው እና ወር በገባ የመጀመሪያው እሁድ በመላ ሀገሪቱ  የሚከናወነው የጽዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ ከተማ ስቴድየም እና የኦሮሞ ባህል ማከል አካባቢ ተከናውኗል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች የተሳተፉበት የፅዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ ኦሮሞ ባህል ማእከልና አካባቢው የተካሄደ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ስቴድየም ደግሞ የከተማው ነዋሪዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የተለያዩ ተቋማት የጽዳት ስራውን አከናውኗል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርአሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ሴፈዲን መሀዲ ንጽህናው በተጠበቀ አካባቢ የሚኖርና  በጥሩ አስተሳሰብ የተገነባ ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጽዳት መረኃግብሩ የተሳተፉ አካላትም አካባቢን ከቆሻሻ ጽዱ በማድረግ ጥላቻና መጥፎ አመለካከቶችን ማስወገድ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡