በእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

በእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው::

በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ  እየተካሄደ ባለው በዚህ ኮንፈረንስ በእናቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ፣ በስነ ተወልዶና በቤተሰብ እቅድ እንዲሁም ከስርዓተ ምግብ ጋር በተያያዘ ጥራት ያለው የጤና አግልግሎት መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ የምርምር ባለሞያዎች  በተለይም በእናቶች፣ በጨቅላ ሕፃናት፣ በሥርዓተ ምግብ እና በክትባት ዙሪያ የሚሰሩ ጥናቶች በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲያግዙ ማድረክ የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ በአጠቃላይ ከ41 በላይ የጥናት ሥራዎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡

ጥናቶቹ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕፃናት ጤናን ለመጠበቅ እና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እንደ ግብዓት የሚጠቅሙ መሆናቸው ተገልጿል።

ለውይይት የቀረቡት ጥናቶችም የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ለሚሠራው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም በግብዓትነት  የሚያገለግሉ  የምርምር ሥራዎች መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

እነዚህን የጥናት ውጤቶች መነሻ በማድረግም በቀጣይ በእናቶች፣ ሕፃናት እና በአፍላ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡