ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልእኮ በብቃት ማስፈም እንዲችል አዋጅና ደንቦችን የሚያሻሽል ረቂቅ አዘጋጀ

የፌዴራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የተሰጠውን ተልእኮ በብቃት ማስፈም እንዲችል አዋጅና ደንቦችን የሚያሻሽል ረቂቅ አዘጋጅቷል፡፡

አዲስ በመዘጋጀት ላይ ካለው የከፍተኛ መንግሥት ባለስልጣናት የስነ ምግባር ደንብ በተጨማሪ በሀብት ማሳወቅና ማስመዝገቢያ እንዲሁም የስነምግባር መኮንኖች አሰራርን ለመወሰን በወጣው ደንብ ላይ ረቂቅ ማሻሻያዎች መዘጋጀታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ የባለፈውና የቀጣይ በጀት አመቱን እቅድና አፈጻጸም አስመልክቶ በጋራ ከሚሰሩ የጸረሙስና ጥምረት አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሀብት ማስመዝገብ ላይ ያለው አፈጻጸም ደካማ መሆኑ በመድረኩ ተነስቶ ተገምግሟል።

ኮሚሽኑ በስሩ የምርመራና አቃቤ ህግ ስራን አቀናጅቶ አለመስራቱ  ውጤታማ እንዳይሆን  አድርጎታል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ሙስና በሃገሪቱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት 3ኛው ሃገር አቀፍ የሙስና ቅኝት  ጥናት መጀመሩን  ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሀገራዊ የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ የዝግጅት ሂደት መጀመሩንም ነው ኮሚሽኑ የገለፀው።

የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም እንዳሉት የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅን ጨምሮ ተቋማዊ የውስጥ አሠራርን የተመለከቱ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

ብልሹ ስነ ምግባርንና ሙስናን የመዋጋቱ ስራ በተቋማዊ አደረጃጀት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የህብረተሰቡንና የሚመለከታቸው አካላትን የተቀናጀ ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡