የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የልጃገረዶች ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይከበራሉ

የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ጨዋታዎች በዋግ ኽምራ፣ በላል ይበላ እና በቆቦ ከዛሬ ነሐሴ 16 እስከ 21/2011 ዓ.ም ይከበራሉ።

በበዓሉ ለመታደም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ ትናንት ማምሻውን ሰቆጣ ከተማ ገብቷል።

ለልኡካኑ የሰቆጣ ከተማና እና አካባቢዋ ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። የየወረዳዎቹ ሻደይ ባህላዊ ተጫዋች ቡድኖችም በባህሉ ዜማና ጨዋታዎች ታጅበው ነው የአቀባበል ያደረጉላቸው። ሰቆጣም ከዋዜማው ጀምሮ የሻደይ ጨዋታን መከወን ጀምራለች።

የዘንድሮው የሻደይ በዓል "ሻደይ ባህላችን ለዘላቂ ልማትና ሰላማችን" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚከበረው።

የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የልጃገረዶች ጨዋታዎች ባለፈው ዓመት በክልል ደረጃ ባሕር ዳር ላይ መከበሩ ይታወሳል። በዚህ ዓመት ደግሞ ከክልል ባለፈ አዲስ አበባ ላይም እየተከበረ ነው። በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችም እንደሚከበር ታውቋል።

በአዲስ አበባ በፓናል ውይይት በየክፍለ ከተሞች ሲከበር የቆየው በዓሉ የፊታችን ነሐሴ 19/2011 ዓ.ም በሚሊኒዬም አዳራሽ ይከበራል፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ለማስፈርም ጥረቱ ቀጥሏል።