የአሸንዳ /አውርስ በዓል በትግራይ ክልል እየተከበረ ነው

የአሸንዳ /አውርስ በዓል በትግራይ ክልል በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

በዓሉ “አሸንዳ/አውርስ የሰላም፣ አንድነትና ልማት ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመከበር ላይ ነው የሚገኘው።

በዓሉ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች እና የገጠር ወረዳዎች በሙሉ በመከበር ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በአሁኑ ሰዓትም በክልል ደረጃ በዓቢይ ዓዲ ከተማ እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት፣ በትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አብረሃም ተኸስተን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልል እና የፌደራል የስራ ሃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በዓቢይ ዓዲ ከተማ በመከበር ላይ በሚገኘው በዓል ላይም ከሰቆጣ የመጡ ልኡካንም በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

አሸንዳ/አውርስ በዓል ከ8 ሰዓት ጀምሮ በክልል ደረጃ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል አመራሮች በተገኙበት በመቐለ ከተማ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም ይጠበቃል።

በትግራይ ክልል በነሃሴ ወር የሚከበረው የአሸንዳ፣ ማሪያ እና ዓይኒ-ዋሪ በዓላት የክልሉን ባህል፣ ትውፊትና የቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ስራ የሚሰራበት ፕሮግራም ነው።

አሸንዳ እና ማሪያ ከነሃሴ 16 ጀምሮ የሚከበር ሲሆን፥ ዓይኒ-ዋሪ ደግሞ ነሃሴ 24 2011 ዓ.ም በአክሱም ከተማ እና አካባቢው የሚከበር የልጃ ገረዶች በዓል ነው።

በዓሉ በህዝቦች መካከል ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር እንዲኖር ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ለቱሪዝም መስህብነት በማገልገል ለኢኮኖሚው አስተዋዕኦ እንዳለው ይታወቃል።

እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ አሸንዳ/አውርስ በዓል የፊታችን ነሃሴ 26 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የሚከበር ይሆናል።