በተያዘው ክረምት ወራት በጎርፍ አደጋ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊጠቁ እንደሚችሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ

በክረምት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊጠቁ እንደሚችሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ብሄራዊ ሜትዎሮሎጂ እና የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን በጋራ በመሆን በሀገሪቷ የክረምት ወቅት ሊፈጠር ይችላል ተብሎ በሚታሰበው ቅጽበታዊ ጎርፍ አደጋ እና ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ በሚዘንብ ዝናብ፣ በወንዞች እና ግድቦች መሙላት ምክንያት በተለያዩ የሃገሪቷ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ በዚህም የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የጎርፍ አደጋው የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ እና ለመከላከል በፌደራል እና በክልል ደረጃ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ለቅድመ ጎርፍ መከላከል እና በጎርፍ ወቅት 1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ ሊጠቁ እንደሚችሉ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ከ23 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ላይ በጎርፍ አደጋ ጉዳት እንደደረሰም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የብሄራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ የ2011 የክረምት የአየር ፀባይ አዝማሚያን በተመለከተ በግንቦት ወር መረጃውን ለህዝብ ተደራሽ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት በአብዛኛው ሃገሪቷ ክፍል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሚቀጥሉት የክረምት ወራት ደግሞ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚከሰት እና በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ያጋጥማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሄራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ሃ/ማርያም ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ቆቃ፣ መልከዋከና፣ ግልገል ጊቤ፣ ተከዘ እና ሌሎች ግድቦች ላይ እየተከሰተ ባለው የውሃ መሙላት ሳቢያ የጎርፍ አደጋ እንሚያጋጥማቸው ተገልጿል፡፡

ግድቦቹ በመሙላታቸው በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ እንደሚገኙ የገለጹት የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው በግድቦቹ አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያጋጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የጎርፍ ስጋት ወደሌለባቸው አካባቢዎች መሄድ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡