ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በኮሪያ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ሀውልት ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በኮሪያ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ሀውልት ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው የደቡብ ኮርያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን በኮርያ ጦርነት ወቅት ለወደቁ የኢትዮጵያ ሰማዕታት መታሰቢያ በሆነው በሴውል ብሄራዊ የመቃብር ቦታ ጉንጉን አበባ በማስቀመጥ ነው የጀመሩት፡፡

በኮሪያ ጦርነት ኢትዮጵያ ከ6 ሺህ በላይ ሰራዊት ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን፣ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም መሰረት የጣለ ክስተት ነወ ተብሏል።

የኢትዮጵያና የኮርያ ግንኙነት በ1940ዎቹ ንጉሠ ነገሥታት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክቡር ዘበኛ ሰራዊታቸውን ወደ ኮርያ የተባበሩት መንግሥታት ኃይልን እንዲቀላቀሉ በላኩ ወቅት የተጀመረ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚነስትር ዐብይ የኮሪያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዪኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር ጋርም የተወያዩ ሲሆን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲው ኢትዮጵያውያንን በማስተማር እና በማሰልጠን ሀገሪቱ ወደ ብልጽግና በምታደርገውን ሽግግር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንትናው ዕለት በደቡብ ኮርያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።