የሰላም ሚኒስትሯ ከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር በእምነት ተቋማት ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ መከሩ

የሰላም ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያ ከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር በእምነት ተቋማት ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ መከሩ።

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እና የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ከብጹአን ሊቃነጳጳሳት ጋር በሀገር ደረጃ እና በእምነት ተቋማት ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ መከሩ፡፡

በውይይቱ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ለሀገር አንድነትና ሰላም የበኩሏን አስተዋጽኦ ስታበረክት መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

በአገሪቷ በተለያዩ ጊዜያት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ መቆየታቸውንና ቤተክርስቲያኗም ተልዕኮዋን ለመፈጸም እንቅፋት እየገጠማት መሆኑን ጭምር ለሚንስትሯ አስረድተዋል፡፡

በእምነት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችም ከጊዜ ወደጊዜ እየገዘፉ በመምጣታቸው መንግስት በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ድርጊቶቹ እንዳይበራከቱ ሊያደርግ ይገባዋልም ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሀገር ሰላም ግንባታ ላይ ላበረከተችው አስተዋጽኦ በማመስገን፤ቤተክርስቲያኗ ችግሮች ባጋጠሟት ጊዜ ሁሉ በአስተዋይነትና በአርቆ አሳቢነት ላለፈችበት መንገድም መንግስት ትልቅ አክብሮት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በእምነት ተቋማት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች እና የእምነት ተቋማቱን በተለያዩ መንገዶች የማወክ እንቅስቃሴዎች በአንድ ወይም በሁለት ተቋማት ላይ ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን ሁሉንም እምነቶች ኢላማ ያደረጉ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ የእምነት ተቋማት በሀገር ግንባታ ላይ የሚታይና የሚነበብ ታሪክ ያላቸው በመሆኑ በተቋማቱ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችም ሀገርን የማፍረስ ተልዕኮ ያነገቡ ሀይሎች የሚፈጽሙት በመሆኑ መንግስትና የሀይማኖት ተቋማት በቅንጅት መከላከል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

መንግስትም በሀገር ደረጃ ዴሞክራሲን ከማስፋት ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባርን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የሰላም ሚኒስትሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንዳስገነዘቡትም አዲሱን ዓመት ያሉብንን በርካታ ሀገራዊ ችግሮች አራግፈን ወደ ሰላም ዓመት እንድናመራ መላው ኢትዮጵያውያን፣ የእምነት ተቋማት፣ መንግስት እና የሚመለከታቸው ሁሉ ለሰላም መስፈን በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡